በሐረሪ ክልል የሚገነባው የኢኮ ቱሪዝም ፓርክ የዘርፉን እድገት እንደሚያፋጥን ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ እየተገነባ የሚገኘው የኢኮ ቱሪዝም ፓርክ ቱሪስቶችን በመሳብ የዘርፉን እድገት እንደሚያፋጥነው የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተፅፎ ለህትመት የበቃው የመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ ገቢ ለክልሎች የቱሪዝም ስፍራዎችን መጠበቂያና ማስፋፊያ እንዲውል አቅጣአጫ መስጠታቸው ይታወቃል፡፡
በዚህም መሠረት በሐረሪ ክልል ከመፅሐፉ ሽያጭ ገቢ የኢኮ ቱሪዝም ፓርክ ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡
ክልሉ ከመፅሃፉ ሽያጭ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ያስገባ ሲሆን፥ ከመንግስት በጀት ተጨምሮበት በ141 ሚሊየን ብር ፓርኩ እየተገነባ ይገኛል፡፡
ግንባታውም 58 በመቶ መድረሱን የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃ ኃላፊና የፓርኩ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ አሚር ረመዳን ተናግረዋል፡፡
በ2 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ኢኮ ፓርኩ፥ የጅብ ትርዒት ማሳያን ጨምሮ የስዕል ማሳያ፣ ሙዚየሞች፣ የባህላዊ ቁሳቁስ መሸጫና ማሳያዎች እንዲሁም ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ማዕከላትን በውስጡ ይዟል።
በቲያ ኑሬ