Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ስለሺ በቀለ(ዶ/ር ኢ/ር) ከተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መከሩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ከተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደሩ ከካሊፎርኒያ የምክር ቤት ተወካይ ቴድ ሊዩን ጋር የተወያዩ ሲሆን ÷ በተለያዩ ጉዳዮች ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ ስላለው የፀጥታ ሁኔታና ለሰላም ስለሚደረገው ጥረት፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ምክንያት በደረሰው ችግር ለተጎዱ ዜጎች ስለሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ እና ኢትዮጵያ ከአጎዋ በመገለሏ ስለሚያስከትላቸው ጉዳቶች ይገኙበታል።

እንዲሁም አምባሳደር ስለሺ(ዶ/ር ኢ/ር) ÷ በአሜሪካ ዲፓርትመንት የኢኮኖሚና ቢዝነስ ጉዳዮች ቢሮ የበጎ ፈቃደኞች እና የፋይናንስ ጉዳዮች ተጠባባቂ ምክትል ረዳት ፀኃፊ ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋርም መክረዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያን የዋጋ ንረት በሚያባብሱ ወቅታዊው የጥቁር ገበያ እና ኢትዮጵያ ስላጋጠሟት ሌሎች የፋይናንስ ፈተናዎችም ላይ ተወያይተዋል፡፡

በተመሳሳይ የአሜሪካ ረዳት የንግድ ተወካይ ኮንስታንስ ሃሚልተን ጋር የተገናኙት አምባሳደሩ ፥ ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ መመለስ ስለሚቻልበት ሁኔታ በስፋት መወያየታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከአጎዋ መነጠል በተለይም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶችና ወጣቶች የስራና ኑሮ መብት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ፤ ውሳኔው በተለይ የአሜሪካ ባለሃብቶች ላይ ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ እንዲሁም በግጭት እና በአደጋ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም እንቅፋት መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

አምባሳደር ስለሺ (ዶ/ር ኢ/ር) በቅርቡ በአሜሪካ የአልጄሪያ አምባሳደር ሆነው ከተሾሙት አምባሳደር ሳብሪ ባኦንካደምን ጋር በመገናኘት በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ጥቅሞች ላይ መወያየታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

አምባሳደር ስለሺ(ዶ/ር ኢ/ር) ÷ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንዲሁም የአምባሳደሩ አማካሪ እና የዩ ኤን ዲ ፒ ተወካይ ባሲል ማሴ ጋርም መክረዋል፡፡

በውይይታቸው ÷ ስለትጥቅ ማስፈታት፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ስለመመለስ ስራ፣ መልሶ ስለ መገንባት እና ለትግበራው አስፈላጊ ግብአቶችን የማሰባሰብ ስራን አስመልክቶ የመከሩ ሲሆን÷ለዚህም በቂ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.