በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ርክክብ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በክልል መዋቅር ለሚገኙ የመንግስት ሠራተኞችና አመራሮች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ መሬት ርክክብ በይፋ ተጀምሯል።
የዕድሉ ተጠቃሚዎች ከክልሉ እንደገና መደራጀት ጋር በተያያዘ መኖሪያ አካባቢያቸውን ቀይረው በአዲሱ ክልል ማዕከል ከተሞች የሚኖሩ የክልል መዋቅር ቋሚ የመንግስት ሠራተኞችና አመራሮች መሆናቸው ተገልጿል።
የመሬት ርክክቡ በሆሳዕና ከተማ ሲጀመር መስፈርቱን ያሟሉ አምስት የመኖሪያ ቤት ህብረት ሥራ ማህበራት የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በወቅቱ እንደተናገሩት÷ በክልሉ ከተሞች የከተሜነት ደረጃን ለማሻሻል በትኩረት እየተሠራ ነው።
በከተሞች የነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል ከተያዙ ስትራቴጂዎች አንዱ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት በመሆኑ ነዋሪዎች በአቅማቸው የመኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ የተለያዩ አማራጮችን በማስቀመጥ እየሠራ ነው ብለዋል።
በክልሉ ሁሉም ማዕከላት በመኖሪያ ቤት ማህበር ተደራጅተው መስፈርቱን የሚያሟሉ የክልል መዋቅር የመንግስት ሠራተኞችና አመራሮች በበጀት ዓመቱ መሬት እንዲያገኙ ይደረጋልም ነው ያሉት።
ከአቅም ጋር በተያያዘ በዚህ ማዕቀፍ መጠቀም የማይችሉ በሌሎች አማራጭ ማዕቀፎች በሚጠቀሙበት አግባብ እንደሚሠራ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።