የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድር ምክር ቤቱ በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አስተላለፈ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔ ማስተላለፉን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አምሪያ ስራጅ ገለጹ።
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሔድ የነበረው መደበኛ ስብሰባ ማጠናቀቁን የገለጹት ኃላፊዋ፤ በአጀንዳነት ከቀረቡለት ጉዳዮች ውስጥ የ77 የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን መርምሮ ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቅሰዋል።
በክልሉ በሰባት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ የሰው ኃይል የመዋቅር ጥናት ልዩ ልዩ አዋጆች እና ደንቦች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔ መተላለፉንም ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት 10 የተለያዩ አዋጆችና 10 ደንቦችን በመመርመር አዋጆቹ ለክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርቡ መስተዳድር ምክር ቤቱ የወሰነ ሲሆን፤ ደንቦቹ የቀጣይ የስራ መመሪያ እንዲሆኑ ውሳኔ ማስተላለፉን ተናግረዋል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ ከተመለከታቸው ጉዳዮች ውስጥ የመንግስት ሰራተኞች የስራ ስምሪት እና የአመራር ስምሪት የጥናት ሰነድ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት መጠቆማቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።