Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትና የሴቶች ልማት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በ68ኛው ዓለም አቀፍ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትና የሴቶች ልማት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡

ጉባዔው “ድህነትን በመቅረፍ፣ ተቋማትን በማጠናከርና በሥርዓተ ጾታ እይታ ፋይናንስን በማጎልበት የሥርዓተ ጾታ እኩልነት ስኬትን ማፋጠንና ሁሉንም ሴቶችና ልጃገረዶች ማብቃት” በሚል መሪ ሃሳብ ነው በኒውዮርክ እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

በመድረኩም ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከገንዘብ ሚኒስቴር የተወጣጣ ልዑክ እየተሳተፈ ነው፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላት በጉባዔው የስብሰባ አጀንዳ በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች እና የጎን ለጎን ምክክሮች ላይ እየተሳተፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህ መሰረትም “ለጾታ እኩልነት ሃብትን ማሰባሰብ፣ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ማብቃት” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክክር መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በተመሳሳይ “የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማስፈን እና ሁሉንም ሴቶች እና ልጃገረዶች ለማብቃት ተቋማትን በማጠናከርና የገንዘብ ድጋፍን በማሳደግ ረገድ ያሉ መልካም ተሞክሮዎች” በሚል በተዘጋጀው መድረክ ላይም ተገኝተዋል፡፡

በሌላ በኩል በዩኒሴፍ እና በዩኤንኤፍፒኤ የጋራ ትብብር የሚካሄደውና የህጻናት ጋብቻ ማቆም ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት በቀጣይ 5 ዓመታት የሚተገበር 3ኛው ዙር ፕሮግራም ይፋ በተደረገበት መድረክ መታደማቸውንም ተጠቁሟል፡፡

የሀገራት ሪፖርት በሚቀርብበት ዋናው ፕሮግራም ላይም በመገኘት የኢትዮጵያን ሪፖርት በተሳካ ሁኔታ ማቅረብ እንደተቻለም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.