ኢትዮጵያ በዲጂታል የፋይናንስ ስነ-ምህዳር እድገት እያስመዘገበች ነው – አቶ ማሞ ምህረቱ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በዲጂታል የፋይናንስ ስነ-ምህዳር እድገት እያስመዘገበች ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
አፍሪካ ቢዝነስ ባወጣው የባንክ ገዥው ጽሁፍ፤ ሀገሪቱ በዲጂታል ፋይናንስ ስነ-ምህዳር እያስመዘገበች ስላለው እድገት አብራርተዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2021 ላይ የጀመረው ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያዎች ስልት ከፖሊሲ ማሻሻያነት በዘለለ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ ቅርፅ ወደ አንድ የበለጠ አካታች፣ ቀልጣፋ እና የበለፀገ ገፅታ እንደለወጠ ገልጸዋል።
በፈረንጆቹ 2024 የስትራቴጂው የመጀመሪያ ምዕራፍ አፈጻጸም ወደ ፍጻሜ እየተቃረበ እንደመሆኑ መጠንም በመጀመሪያው የፋይናንስ ሥነ-ምህዳር የሸፈንናቸውን አካባቢዎች፣ የተሻገርናቸውን መሰናክሎች እና ወደ ዲጂታል ያደረግናቸው ጉልህ እመርታዎች ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መሪነት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ከተቋቋመው ቤተርዛን ካሽ አሊያንስ ጋር በመታገዝ፣ ስልቱ በሀገሪቱ አነስተኛ የጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት እያመጣ መሆኑንም አመላክተዋል።
ከመግቢያው ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ የክፍያ ሥነ ምህዳር፣ ሰፊ እና ውስብስብ፣ ወደ ዲጂታል ሥነ ምህዳር ለመሸጋገር በርካታ ፈተናዎች የነበሩበት እንደነበርም አንስተዋል፡፡
እነዚህ ተግዳሮቶች የመሠረተ ልማት ጉድለቶች፣ የዲጂታል ማንበብና መጻፍ ክፍተቶች፣ የቁጥጥር መሰናክሎች እና እያደገ ያለው የፋይናንስ የሥርዓተ-ፆታ አካቶ ክፍተት ይገኙበታል ብለዋል።
ይሁንና በክፍያ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ግልጽነት፣ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ እድገት እና ዲጂታል ክፍያዎችን በኃላፊነት መጠቀም የበለጠ በቅልጥፍና በመራመድ ለፋይናንሺያል አብዮት መንገድ እንደከፈቱ አስገንዝበዋል።