Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሃይማኖት አባቶች ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሃይማኖት አባቶች ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በጋምቤላ ከተማ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ተወያይተዋል።

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የሃይማኖት አባቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ለሠላም ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል።

የክልሉ መንግስት ሠላሙን በዘላቂነት ለማስቀጠል የተለያዩ የህግ ማስከበር ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በመሆኑም የክልሉን ሰላም በማፅናት ለተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መሳካት የሃይማኖት አባቶች ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ በበኩላቸው÷ የሃይማኖት አባቶች ማህበረሰቡን የሚያቀራርቡ ገንቢ ተግባቦቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በተለይ የኃይማኖት አባቶች ስለ ሰላም አስፈላጊነት ለህብረተሰቡ እየሰጡት ያለውን ግንዛቤ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውንም የክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች በሰጡት አስተያየት÷ ሠላም፣ ፍቅር እና አንድነትን ለተከታዮቻቸው በማስተማር የክልሉን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እንደሚሰሩ አብራርተዋል።

የሃይማኖታቸው አስተምህሮ ሰላምን የሚሰብክ በመሆኑ ስለ ሰላም አስፈላጊነት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.