Fana: At a Speed of Life!

የአገልግሎትና አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለማሻሻል ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል – ም/ጠ/ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ችግሮችን በመሰረታዊነትና በዘላቂነት ለማሻሻል ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የተቋማት ሃላፊዎች በተገኙበት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ የሶስት ወራት የቅድመ ዝግጅት ተግባራት የግምገማ መድረክ ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር መሰረታዊ ችግሮች ስለነበሩበት ሀገራዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ግቦች በሚፈለገው ልክ እንዳይሳኩ አድርጓል ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ሳይፈቱ የቆዩ የልማትና የአገልግሎት ችግሮችን በመቅረፍ የብልፅግና ጉዞን ለማሳካት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ከዳር ለማድረስም የተቋማት የማስፈጸም አቅም ደካማ መሆኑ ፈታኝ ሆኗል ነው ያሉት።

በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የወጡ እቅዶችንና ፖሊሲዎችን ለማሳካት የመንግስት የማስፈጸም አቅምን ማሻሻል ወሳኝ እንደሆነ ታምኖ ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል።

ለዚህም በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ከተያዙ ዋና ዋና ጉዳዮች የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደርን ማሻሻል እንደሚገኝበት መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ማሻሻያ ለማምጣት የህግ ማዕቀፎች የተዘጋጁ ሲሆን በቅርቡ ፀድቀው በይፋ ወደ ትግበራ ይገባሉ ብለዋል።

ይህንን ሀገራዊ ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ በእቅድ መመራት፣ የራሱ የሰው ሃይልና አደረጃጀት መድቦ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ የተቋማት አመራሮች ለተፈጻሚነቱ ጥብቅ ክትትል እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሲተገበር የቆየው ሲቪል ሰርቪስ ሀገራችንን የማይመጥንና በርካታ ስብራቶች ያሉበት ነው ብለዋል።

የለውጡ መንግስት ይህንን ሀገራዊ ችግር በትኩረት በመቃኘት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም አስፈላጊ ረቂቅ ፖሊሲዎችና የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ከጥር 2016 ዓ.ም ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.