የፊቼ ጨምበላላ በዓል በሃዋሳ ጉዱማሌ በድምቀት እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ በዓል በሃዋሳ ከተማ ጉዱማሌ በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
በትናንትናው ዕለት ዋዜማው ” የፊጣሪ” በዓል የተከበረ ሲሆን÷በዛሬው ዕለት ደግሞ በአደባባይ የፊቼ ጨምበላላ በዓል እየተከበረ ይገኛል ።
የብሔሩ ተወላጆችም ከጠዋቱ 12 ሰዓት አስቀድመው ከያሉበት ቦታ ወደ ጉዱማሌ (የበዓሉ ማብሰሪያ ስፍራ) በመምጣትና በአንድ ላይ በመሰባሰብ በዓሉን በማክበር ላይ ይገኛሉ ።
በአሁኑ ሰዓትም የብሔሩ ተወላጆች በዓሉን በቄጣላ ጭፈራ ፤ በፋሮና በሌሎች ባህላዊ ክዋኔዎች አጅበው እያሳለፉ ናቸው፡፡
በባህላዊ አልባሳቶቻቸው የደመቁት የበዓሉ ታዳሚያን በአብሮነትና በፍቅር የሚያሳልፋበት ዕለት ነው ።
በዓሉ ህፃናት ቢያጠፋ እንኳን የማይቀጡበት፣ ከብቶች ተደስተው እንዲያሳልፋ በተከለለ ሳር ውስጥ እንዲመገቡ የሚደረግበት፣ መሬት የማይታረስበት፣ እንጨት የማይቆረጥበት እና የተጣሉ ግለሰቦች ታርቀው ያለቂም በቀል አዲስ ዓመትን የሚቀበሉበት ነው፡፡
የፊቼ ጨምበላላ በዓል በአንድነት የሚከበር በመሆኑ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወላጆችም በበዓሉ መታደማቸው ተመላክቷል፡፡
በደብሪቱ በዛብህ ፣ ብርሃኑ በጋሻው ፣ አፈወርቅ እያዩ