በጋምቤላ ያለውን የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት ለማቃለል እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመማሪያ መጻሕፍት እጥረትን ለማቃለል ከ228 ሺህ በላይ መጻሕፍት ኅትመት እየተከናወነ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ኅትመቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም ዘንድሮ ለ1ኛና 2ኛ ሳይክል ተማሪዎች እንደሚሠራጭ የገለጹት የቢሮው ኃላፊ ላክዴር ላክባክ÷ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የሚሆን 98 ሺህ መጻሕፍት ታትሞ መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
በኅትመት ላይ ከሚገኘው መጻሕፍት 164 ሺህ 684 ለአካባቢው ተማሪዎች እንዲሁም 63 ሺህ 714 ያህሉ በስደተኛ ጣቢያ ለሚገኙ ተማሪዎች እንደሚሠራጭ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለውን የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት ለማቃለል 103 ሚሊየን ብር መመደቡን ጠቅሰው÷ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ቀደም ብሎ 216 ሺህ 767 መጻሕፍት መሰራጨቱን አስታውሰዋል፡፡