በመዲናዋ ከቤት ግብር ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቤት ግብር ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አደም ኑሪ እንደገለፁት÷ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ448 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የቤት ግብር ከፍለዋል።
ከዚህ በፊት ከዘርፉ ይሰበሰብ የነበረው ከ300 ሚሊየን ብር ያልበለጠ እንደነበር የገለፁት ሃላፊው ÷ በአሁኑ ወቅት 6 ነጥብ 45 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በመዲናዋ የሚሰበሰበውን ገቢ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችን የማጎልበት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ቢሮው በቤት ግብር ዙሪያ ያሉ ችግሮችን የማስተካከል ስራ እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የቤት ግብር ያልከፈሉ ሰዎችን ተከታትሎ የማስከፈልና እርምጃዎችን የማጠናከር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመዲናዋ በቤት ወይም በከተማ ቦታ ኪራይ እና የቤት ግብር አዋጅ መሰረት የጣራ እና ግድግዳ የግብር ክፍያ መተግበር ከጀመረ ከ1 ዓመት በላይ የሆነው ሲሆን÷ በዚህም በመዲናዋ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ አፓርትመንቶች እና ህንጻዎች ወደ ቤት ግብር ስርዓት እየገቡ ይገኛሉ።