የትግራይ ክልል ምክር ቤት 6ኛው ክልላዊ ምርጫ እንዲካሄድ ወሰነ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት የ2012 ዓ.ም ክልላዊ ምርጫ ህግን ተከትሎ በወቅቱ እንዲካሄድ በሙሉ ድምፅ ወሰነ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 5ኛ የስራ ዘመን 7ኛ አስቸኳይ ጉባኤ 6ኛው ክልላዊ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል።
በተጨማሪም ኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ ላይም ተወያይቷል።
በዚህ መሰረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሰኔ 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ወር ተኩል እንዲቀጥል መወሰኑን ከትግራይ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በሃገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ መንግስት ስርጭቱን ለመግታት በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።
የቫይረሱ ወረርሽኝም በህዝቡ ጤንነትና ደህንነት ላይ ስጋት መፍጠሩን ተከትሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑም ይታወቃል።
በዚህ ሳምንት መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የፌዴሬሽን ምክር ቤትም አሁን ያሉት የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች የወረርሽኙ ስጋት ተቀርፎ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ እንዲቀጥሉ መወሰኑ የሚታወስ ነው።