Fana: At a Speed of Life!

የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ የምርምር ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ብሔራዊ የትስስር ምክር ቤት ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች ብሔራዊ የትስስር ምክር ቤት መመስረቱን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ብሔራዊ የትስስር ምክር ቤቱ የተመሰረተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ 1298/2015 ወደ ሥራ መግባትን ተከትሎ እንደሆነ ተመላክቷል።

በዚህም ብሔራዊ የትስስር ምክር ቤት ትናንት በትምህርት ሚኒስቴር በተካሄደ መድረክ በትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ሰብሳቢነት መመስረቱ ተገልጿል፡፡

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን የሚያደርገውን ጉዞ ለማፋጠን የትስስር ምክር ቤቱ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡

እንደ ሀገር ከድህነት ለመውጣት በምርምር የተደገፈ ዕውቀት መር ሀገራዊ ኢኮኖሚን መገንባት እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለዚህም ተቋማት ለምርምር ሥራ በቂ በጀት መመደብ እንደሚገባቸው ማስገንዘባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ምክር ቤቱ ከኢኮኖሚ ሴክተር መሪ መስሪያ ቤቶች፣ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበር፣ ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ማህበር፣ ከኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች የተውጣጡ 22 አባላት እንዲኖሩት ተወስኗል።

ምክር ቤቱ የትስስሩ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን የማስቀመጥ፣ ሂደትና አፈጻጸም በበላይነት የመከታተልና የመገምገም፣ በወል እና በተናጠል መተግበር የሚገባቸውን የትስስር ጉዳዮች የመለየት፣ የትስስር ስራን የሚያግዙና የሚያማክሩ አካላትን እና ታዋቂ ግለሰቦችን እንደ አስፈላጊነቱ በምክር ቤቱ ስብሰባዎች ላይ የማሳተፍ እና እውቀትና ልምዳቸውን እንዲያጋሩ የማድረግ ሃላፊነት ተሰጥቶታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.