Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በዚህ አመት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረው ብድር ወደ ዜሮ ወረደ- ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዚህ አመት የመንግስት ብድር ወደ ዜሮ መውረዱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ ይህንን የገለጹት በዛሬው ዕለት በተጀመረው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም ላይ ነው።

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ እንደ ዋጋ ንረትና የውጪ ምንዛሬ እጥረት ባሉ በርካታ ችግሮች ሲፈተን እንደነበር አስታውሰው÷ ችግሮቹን ለመፍታት ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባቷን ተናግረዋል።

ማሻሻያውም የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ አካታችነት እና ተገዳዳሪነት ማሳደግ፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት መፍታት፣ የውጪ ንግድን እና የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንዲሁም የዋጋ ንረት መቆጣጠርን ያለመ መሆኑን አመላክተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ራዕዮችን እውን ለማድረግ በተከናወኑ ጥረቶችም የውጪ ምንዛሬ እጥረትን መፍታት እንደተቻለ እና የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፍ የፋይናንስ ዘርፍ እውን መደረጉን ገልጸዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሀገራችንን የፋይናንስ ዘርፍ ተወዳዳሪ እና ገበያ መር፣ የግሉን ዘርፍ ማዕከል ያደረገ ዲጂታላይዝድ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።

በቃለአብ ግርማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.