ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሚደግፍ ፕሮግራም ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረትና አጋሮቹ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሚደግፍ ፕሮግራም ይፋ አድርገዋል፡፡
ፕሮግራሙ የአካባቢውን ኢኮኖሚ ወደነበረበት ለመመለስ እና አነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መልሶ ማቋቋም የሚያስችል መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ከግጭት በኋላ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱትሪዎችን በተሻለ የፋይናንስ አቅርቦት ለመደገፍ ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ይህም በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አምራች ኢንዱስትሪዎች እና በግብርና ማቀነባበር ዘርፍ ላይ የተሰማሩትን በመደገፍ ወደ ምርትና ምርታማነታቸው መመለሰ ያስችላል ተብሏል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ ሀሰን ሙሀመድ÷ ፕሮግራሙ የአውሮፓ ህብረት፣ ኔዘርላንድስ እና ጀርመን ቀጣይነት ባለው መልኩ ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ ያሳያል ብለዋል፡፡
በሴቶችና ወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ልዩ ጠቀሜታ እንዳለው መናገራቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በበኩላቸው÷ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር፣ ኢኮኖሚው እንዲያገግም በማድረግ እና ሰላምን በማስፈን ረገድ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡