የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጎንደር ከተማ ለተባባሪ አካላት ስልጠና እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጎንደር ክላስተር በአጀንዳ ማሰባሰብና ምክክር ላይ የሚሳተፉ የማህበረሰብ አባላትን ለመመልመል የሚያግዙ ተባባሪ አካላት ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ ጎልተው የሚታዩ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሒደት አዲስ አበባንና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በ10 ክልሎች ተሳታፊዎችን ለይቷል፤ ሌሎች በርካታ ውጤታማ ተግባራትንም አከናውኗል ብለዋል፡፡
በአማራና በትግራይ ክልሎች ኮሚሽኑ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ያከናወናቸውን ተግባራት ሳያከናውን መቆየቱን ጠቁመው÷ ለዚህም ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ጦርነትና በመሣሪያ የታገዙ ግጭቶች መሆናቸው አስረድተዋል፡፡
በምክክር ሒደቱ በየደረጃው ተሳታፊ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ የመለየቱ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን በስልጠናው የተሳተፉ ተባባሪ አካላት ሕዝባዊና ሀገራዊ ሃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በጎንደር ከተማ እየተሰጠ በሚገኘው የጎንደር ክላስተር ተባባሪ አካላት ስልጠና ከ75 ወረዳዎች የተውጣጡ ከ500 በላይ ሰልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡
ተባባሪ አካላት ለሶስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና አካታችና አሳታፊ በሆነ አካሄድ ተሳታፊዎችን ስለሚለዩበት ሥነ-ዘዴ ግንዛቤ ይጨብጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡