የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት ወንጀልን ለመቀነስ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ሥርቆት ወንጀልን ለመቀነሰ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል።
በአገልግሎቱ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ሥራ አስፈጻሚ ገበየልህ ካሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ባለፉት ጊዜያት ከጸጥታ አካላት ጋር በተከናወነ ሥራ የመሰረተ ልማት ሥርቆት ወንጀልን መቀነስ ተችሏል።
ይሁን እንጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በባለሙያና በጸጥታ አካላት ብቻ ማስጠበቅ እንደማይቻል ነው የገለጹት፡፡
ስለሆነም ለግል ጥቅም ሲባል የሚፈጸመውን የመሰረተ ልማት ዝርፊያ ለመከላከል ማሕበረሰቡ የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ከማሕበረሰብ ጋር ተቀራርቦ በመስራት የመሰረተ ልማት ስርቆትን ለመቀነስ በቅንጀት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በስርቆት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ከሚመለከተው አካል ጋር በትብብር እንደሚሰራም ሥራ አስፈጻሚው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
በክብረወሰን ኑሩ