Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና አዘርባጃን በቤት ልማት ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና የአዘርባጃን ቤት ልማት ኤጂንሲ በቤት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመራ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማልን ያካተተ ልዑክ ከአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ አመራሮች ጋር በቤት ልማት ዙሪያ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱም የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጋራ ለመስራት በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ስምምነት ላይ መድርሳቸው ተገልጿል፡፡

የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ በመንግስት መነሻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎለት ቤቶችን እንደሚገነባ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡

በዚህም ከ30 በመቶ እስከ 40 በመቶ ከገበያው የዋጋ ቅናሽ ያላቸውን ቤቶች ለሀገሪቱ ዜጎች በሽያጭ እያቀረበ ገበያ የማረጋጋት ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው፡፡

ኤጂንሲው ከመንግስት የሚያገኘውን መነሻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ገበያ ለማረጋጋት ለሚገነባቸው ቤቶች ግንባታ እንደሚያውልም ተጠቁሟል፡፡

ያገኘውን የበጀት ድጋፍ ለመንግስት የመመለስ ግዴታ የሌለበት ተቋም መሆኑንም የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከቅረብ ጊዜ ወዲህ የሪል ስቴት ገበያውን ለማረጋጋት እያደረገ ላለው ጥረት የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ያለውን ሰፊ ልምድ ለፌዴራል ቤቶች እንደሚያጋራ ተገጿል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲን ልምድና ተሞክሮ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.