Fana: At a Speed of Life!

ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮ አንጻር በውጤት የሚመዘኑበት አሰራር ሊዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮና ቁልፍ የለውጥ አጀንዳዎች አንጻር በውጤት እየተለኩ የሚሄዱበት የአሰራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴዔታ ኮራ ጡሽኔ በመቀሌ እየተካሄደ በሚገኘው የፕሬዚዳንቶች ፎረም ላይ እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ተቋማቱ የሀገሪቱን ችግሮች የሚፈቱ፣ ሥራ ፈጣሪና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የሰው ሃይል ማፍራት እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በለውጡ ጎዳና በፍጥነት ሄደው በዓለም ተወዳዳሪ ተቋማት እንዲሆኑና ተልኳቸውን በሚገባ እንዲወጡ ቁልፍ የለውጥ አጀንዳዎች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

የዩኒቨርስቲዎች እድገት፣ ስኬት እና ውጤት መለካት አለበት ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው÷ ለዚህ የሚረዱ ቁልፍ የውጤት መለኪያ አመላካች መስፈርቶች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።

በዚህም የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶቹ በተዘጋጁት ቁልፍ የውጤት መለኪያ አመላካች መስፈርቶች ላይ ውይይት በማድረግ ከሥምምነት ከተደረሰ በኋላ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ፕሬዚዳንቶቹ ውል የሚገቡ ይሆናል ብለዋል።

በቀጣይ በሚኒስቴሩና በዩኒቨርሲቲዎች የሚፈረመው የውል ስምምነት ሃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት፣ ሪፎርሞቹን ወደ መሬት ለማውረድና በሒደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሚያስችልም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.