የብሪክስ አባል ሀገራት የመሬት ምልከታ ሳተላይት አቅም ለጋራ ጥቅም በሚውልበት ጉዳይ ምክክር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪክስ አባል ሀገራት ብሔራዊ የስፔስ ተቋማት አመራሮች ስብሰባ በሩሲያ ሞስኮ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በስብሰባው በኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻያል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ የተመራ ልዑክ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
የሩሲያ መንግስት የስፔስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዩሪ ቦሪሶቭ÷ ለብሪክስ ነባር እና አዲስ አባል ሀገራት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልክዕት አስተላልፈዋል፡፡
የሁሉም አባል ሀገራት የዘርፉ አመራሮች በስፔስ መስክ በየሀገራቸው እያካሄዱ ያሏቸውን እና በቀጣይ ለመስራት ያቀዷቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመድረኩ አቅርበዋል፡፡
አባል ሀገራቱ በድምር ያላቸውን 1 ሺህ 200 የመሬት ምልከታ ሳተላይት እንደ ምሳሌ በመጥቀስ የየሀገራቱ አቅም በብሪክስ የምስረታ መርሕ ላይ ተመስርቶ ለጋራ ጥቅም በሚውልበት ጉዳይ ላይ በጥልቀት መክረዋል፡፡
የብሪክስ የመሬት ምልከታ ህብረ-ሳተላይት ምስረታ እና መረጃ መጋራት የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት ከተመከረባቸው አጀንዳዎች መካከል ዋነኛው መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
አቶ አብዲሳ ይልማ÷ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ በብሪክስ ማዕቀፍ በዚህ መሰል ስብሰባ ላይ መሳተፏ ልምድ ለማግኘት እና ትብብር ለመፍጠር እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከግንቦት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ያስገባችው የብዝሐ-ሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ እና በቀጣይ ለማምጠቅ ታቅዶ እየተሰራበት ያለው የከፍተኛ ሪዞሉሽን የመሬት ምልከታ ሳተላይት የብሪክስ የመሬት ምልከታ ህብረ-ሳተላይት ምስረታና የመረጃ መጋራት አካል አድርጎ በማቀናጀት የጋራ ተጠቃሚነትን የማሳደግን ጉዳይ እንደምታጤነውም ገልጸዋል፡፡