ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን መሠረተ ልማት ውጤታማ ሥራ እያከናወነች መሆኗ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን መሠረተ ልማት የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት የሚያሻሽል ውጤት እያስመዘገበች መሆኗን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት በሥራ ላይ የተመሠረተ የባለሙያዎች ሌቨር ቤዝድ ፕራክቲሽነርስ አህጉራዊ ስብሰባ “የማይበገር ማኅበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ፤ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች” በሚል መሪ ሐሳብ በአፍሪካ ሕብረት እየተካሄደ ነው።
ሚኒስትር ጫልቱ በዚህ ወቅት፤ ስብሰባው የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ ድህነት ቅነሳንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሐሳቦች በማፍለቅ የጋራ አንድነት እና ቁርጠኝነት የምናሳይበት ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ለሥራ ፈጠራ ችግር ከሆኑት መካከልም፤ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የቴክኖሎጂ አቅም ልዩነት፣ ጂኦ ፖለቲካዊ ግጭት ተጠቃሽ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም የሥራ ድርጅት ጋር በቅርበት እንደምትሠራ ገልጸው፤ መንግሥት ለሥራ ፈጠራ፣ ለዘላቂ ልማት፣ የማይበገር ማኅበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በተለይ በመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ከሥራ ዕድል ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ግቦችን ለማሳካት በመንግሥታት፣ በትምህርት ተቋማት እና በግሉ ዘርፍ መካከል ትብብር መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡