የአልነጃሺ መስጅድ ጥገና ሥራ በቀጣይ ሳምንት እንደሚጀመር ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የታሪካዊው አልነጃሺ መስጅድ ጥገና ሥራ በቀጣይ ሳምንት እንደሚጀመር የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የቱሪዝም ሚስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር በርክ ባራን ጋር በአልነጃሺ መስጅድ ጥገና ሥራ ላይ ተወያይተዋል፡፡
ከአምባሳደሩ ጋር በተደረገ ተከታታይ ምክክርም የአልነጃሺን መስጅድ ለመጠገን የቱርክ መንግስት አስፈላጊውን የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም ደረጃውን የጠበቀ የጥገና ሥራ ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ነው የተጠቆመው፡፡
የጥገና ሠራው በቀጣይ ሳምንት በይፋ እንደሚጀመር መገለጹንም የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የመስጅዱ የጥገና ሥራ ታሪካዊ ይዘቱን ለትውልድ ጠብቆ ማስተላለፍ በሚያስችል መልኩ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡