Fana: At a Speed of Life!

የሳዑዲ ከፍተኛ የቢዝነስ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን ሊጎበኝ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የተመራ 79 አባላትን የያዘ የሳዑዲ አረቢያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን ሊጎበኝ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ÷ ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር የማጠናከር ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።

የልዑካን ቡድኑ ዛሬ ማታ አዲስ አበባ የሚገባ ሲሆን÷ በሶስት ቀናት ቆይታው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የማምረቻ ቦታዎችን ይጎበኛል ተብሏል።

በሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ባለድርሻ መ/ቤቶች በኢትዮጵያ ስላሉት ምቹ የኢንቨስትመንትና ንግድ አማራጮች ገለፃ የሚደረግበት የኢትዮ-ሳውዲ አረቢያ የቢዝነስ የምክክር መድረክም እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በሀይል ማምረት፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በሌሎች ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ያሉትን እድሎች ለመገንዘብ እንደሚፈልግም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና በሳዑዲ አረቢያ አቻው መካከል የመግባቢያ ስምምነት ይፈረማል ተብሎም ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.