Fana: At a Speed of Life!

በእርዳታ ዘላቂ እድገትና ብልጽግናን እውን ማድረግ የቻለ ሀገር የለም – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በእርዳታ የጥገኝነት ጊዜውን ያራዘመ እንጂ ዘላቂ እድገትና ብልጽግናን እውን ማድረግ የቻለ ሀገር የለም ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ፡፡

‘ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር’ በሚል መሪ ሃሳብ በቢሾፍቱ የተካሄደውን ህዝባዊ ውይይትና የልማት ሥራዎች ጉብኝት አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታችና ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አይተናል ብለዋል፡፡

እርዳታ ዕለታዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም ያሉት ሚኒስትሯ፤ በእርዳታ የጥገኝነት ጊዜውን ያራዘመ እንጂ ዘላቂ እድገትና ብልጽግናን እውን ማድረግ የቻለ ሀገር የለም ብለዋል፡፡

ጀግኖች አባቶችና እናቶቻችን በከፈሉት መስዋትነት ነፃ ሀገር ያለን ህዝቦች ነን፤ ይህን ነፃነት በልማት ማጽናት ባለመቻላችን እስካሁን ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ነፃነታችን የተሟላ ሳይሆን ቆይቷል ሲሉ ገልጸዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ያሉንን የመልማት ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህም ለሥራ ገበያው የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎት ምላሽ የሚሰጡ፣ የሥራ ፈጣሪነትን የሚያበረታቱ፣ የኢንዱስትሪ ግንኙነቱን የሚያሻሽሉ፣ ኢንቨስትምንትን የሚስቡ፣ ዓለም አቀፍ ትብብሩን የሚያሳድጉ እንዲሁም የክህሎትና እውቀት ሽግግሩን የሚያዳብሩ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተቀርጸው እየተተገበሩ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አንድ ህዝብ ምርትና ምርታማነቱን አሳድጎ ከተረጂነት ራሱን ማላቀቅ ከቻለ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ነፃነት ከማግኘቱም ባሻገር ካልተገባ የውጭ ተጽዕኖ ነፃ ይሆናልም ብለዋል፡፡

ይህም የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ያጎናጽፋልና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.