በጸጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ 87 የሞባይል ጣቢያዎች ዳግም አገልግሎት መስጠት ጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ ሪጅን በጸጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ 87 የሞባይል ጣቢያዎች ተጠግነው በ42 ወረዳዎች የሚገኙ 83 ቀበሌዎችና ከተሞች ዳግም የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘት ጀመሩ፡፡
በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሩ ጉዱሩ እንዲሁም ቄለም ወለጋ ዞኖች የሚገኙ አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ተጠግነው አገልግሎት አግኝተዋል ነው የተባለው።
እስካሁን በተከናወኑ ስራዎችም በሆሩጉዱሩ 18 ፣ በምዕራብ ወለጋ 19 ፣ በቄለም ወለጋ 17 ፣በምስራቅ ወለጋ 12 ጣቢያዎች እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ 1 ጣቢያ ጥገና ተደርጎ አገልግሎት ማስጀመር መቻሉ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ከዚህ በፊት በተሟላ መልኩ አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ 20 የሞባይል ጣቢያዎች አስተማማኝ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፤ በተቀሩት አካባቢዎችም ጥገናው ተጠናክሮ ቀጥሏል መባሉን ከኢትዮ ቴሌኮም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡