የኮሪደር ልማት አዳዲስ አገልግሎትና ስታንዳርዶችን ያስተዋወቅንበት ብስራት ነው- ከንቲባ አዳነች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሪደር ልማት ስራችን በርካታ አዳዲስ የመሰረተ ልማት አገልግሎት እና ስታንዳርዶችን በአይነት፣ በጥራት እና በውበት ያስተዋወቅንበት ለከተማችንና ለሃገራችን ትልቅ ብስራት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከሜክሲኮ እስከ ሳርቤት ያለው የኮሪደር ልማት ስራችንን አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ገምግመናል ብለዋል።
ስራው ከጥቂት የእርማት ስራዎች በስተቀር የተጠናቀቀ ሌላኛው የኮሪደር ልማት መሆን መቻሉን ገልጸው፤ የኮሪደር ልማት ስራ ትልቅ የመፈጸም ብቃት የታየበት፣ ለየት ያለ የስራ ባህል የተተገበረበት፣ ትብብር እና የመሰረተ ልማት ቅንጅት የተሻሻለበት መሆኑን ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማት በርካታ አዳዲስ የመሰረተ ልማት አገልግሎት እና ስታንዳርዶችን በአይነት፣ በጥራት እና በውበት ለከተማችን ያስተዋወቅንበት ለከተማችንና ለሃገራችን ትልቅ ብስራት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የከተማዋን ስታንዳርድ ለማስጠበቅ እና ለእግረኛ መተላለፊያነት እንዲውል ህንጻቸውን በማፍረስ እና በተሰጣቸው ስታንዳርድ መሰረት እድሳት ያደረጉ ተቋማት፣ የቤትና ህንጻ ባለቤቶች እንዲሁም በተለያየ መንገድ በስራው ላይ ለተሳተፋችሁ እና ለተባበሩ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የከተማችን ነዋሪዎች መንገዶቹን በምንሰራባቸው ጊዜያት ለነበረው የትራፊክ መጨናነቅ እና ለተፈጠሩ መጠነኛ ውጣውረዶች ቅር ሳትሰኙ ላሳያችሁን ትዕግስትና ማበረታቻ ከልብ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ብለዋል።
ይህንን እና ሌሎቹንም ኮሪደሮች በቀሪ ጊዜያት ውስጥ አጠናቅቀን ለህዝባችንን አገልግሎት እንዲውሉ የምናደርግ ይሆናል ያሉት ከንቲባዋ፤ የማንተገብረውን ቃል አንገባም፤ ቃል የገባነውን እንተገብራለን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።