2ተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚያደርጉትን ጉዞ ማስተባበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚያደርጉትን ጉዞ ማስተባበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢና የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ÷ጥሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያካሄዷቸው ሀገራዊ ጥሪዎች ተከታይ ክፍል መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዓላማውም ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከባህልና ታሪካቸው ጋር ማስተሳሰር እንዲሁም በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መነሳሳትን መፍጠር መሆኑን አስረድተዋል።
ይህንንም ለማሳካት ብሔራዊ ኮሚቴው ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በፌዴራል ደረጃ ከሚገኙ መንግስታዊና የግል ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ሁነቱ እስከመጪው መስከረም ወር 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ በመሆኑ ሚሲዮኖች የማስተባበር ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው በበኩላቸው÷በጥሪው ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንን ይበልጥ ከሀገራቸው ጋር ማስተሳሰርና አሻራቸውን ማሳረፍ የሚያስችሉ መርሐ ግብሮች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በመድረኩ ከሶስተኛው ምዕራፍ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ጋር በተያያዘ ለማከናወን የታቀዱ ተግባራትና የሚሲዮኖችን ሚና በተመለከተ ገለጻ መደረጉን የዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡