ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኝ የ220 ኪሎ ሜትር መንገድ ሊገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኝ የ220 ኪሎ ሜትር መንገድ ሊገነቡ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሀገራቱ በፈረንጆቹ ግንቦት ወር 2023 የተፈራረሙትን የ738 ሚሊየን ዶላር የፋይናንስ ስምምነት ተከትሎ ነው ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኘው መንገድ የሚገነባው፡፡
የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ የሽግግር ሕግ አውጪ ምክር ቤት የኢትዮጵያ-ደቡብ ሱዳን ድንበር ተሻጋሪ መንገድ ለመገንባት የተፈረመውን የገንዘብ ስምምነት ማጽደቁ ተጠቁሟል፡፡
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መካከል እያደገ ያለውን ትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነት በማሳየት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል።
ስምምነቱ በጉባዔው በሙሉ ድምጽ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ለፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የመጨረሻ ፈቃድ መቅረቡንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡