የታንዛኒያ ከፍተኛ ወታደራዊ ልዑክ በመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ጉብኝት አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በታንዛኒያ የዘመቻና የስልጠና ሀላፊ ሜጀር ጀኔራል ኢብራሂም ሚካኤልና በአየር ሀይሉ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሻባኒ ባራንጋሽ የተመራ ከፍተኛ ወታደራዊ ልዑክ የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅን ጎበኘ።
በጉብኝቱ÷ የኮሌጁን የመማር ማስተማር ዘዴና በሚቀጥሉት ዓመታት ሊደርስባቸው እየሰራቸው ባላቸው ጉዳዮች ላይ በኮሌጁ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸውና በከፍተኛ አመራሮች ገለፃ ተደርጓል።
ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው÷ ኮሌጁ በቀጣይ በትምህርትና ወታደራዊ ስልጠና መስኩ ከታንዛኒያ ጋር በትብብር በመስራትና ልምድ በመለዋወጥ ያለውን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል፡፡
ሜጀር ጄኔራል ኢብራሂም ሚካሄል÷ ኮሌጁ ተለዋዋጭ የሆነውን የዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ስጋቶችንና ቴክኖሎጂያዊ ለውጦችን በሳይንሳዊ ዘዴ በመተንተን እየሰጠ ላለው ስልጠና ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።
በኮሌጁ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልጸው፤ ኮሌጁ የስትራቴጂክ ዕቅድ በመያዝ የሚያከናውናቸው ተግባራት ለአፍሪካውያን በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም ከኮሌጁ ጋር በትብብር መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለፁት ጄኔራል መኮንኑ፤ በኮሌጁ እየተማሩ የሚገኙ የታንዛኒያ ተማሪዎችንም ማበረታታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡