ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶች ተመዝግበዋል- አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2016 በጀት ዓመት ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
በክልሉ የ2016 በጀት ዓመት የ12 ወራት የልማት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ተካሂዷል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ባለፉት 12 ወራት የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ናቸው፤ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ስኬቶችም ተመዝግበዋል፡፡
ያለውን አንፃራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር በክልሉ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ኃይሎች ጋር መንግስት ባደረገው የሰላም ስምምነት በሰራው ስራ ውጤት መመዝገቡንም ጠቅሰዋል።
ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለሕብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል፡፡