Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የሚስተዋሉ የደንብ ጥሰቶች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ባለሥልጣኑ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ ዘርፎች በሚስተዋሉ የደንብ ጥሰቶች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል አለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ አዲስ አበባ አሁን ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን የማስተናገድ አቅም ገንብታለች፡፡

የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከተማዋ ዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ስብት ማዕከል ሆና እንድትቀጥል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመልክተዋል፡፡

ስለሆነም በመዲናዋ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ላይ የሚስተዋሉ የደንብ መተላለፍ ተግባራትን ለመከላከል በቁርጠኝነነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በመሬት ወረራ፣ በሕገ ወጥ ንግድ፣ በአዋኪ ተግባራት፣ በሕገ ወጥ ማስታወቂያና እርድ እንዲሁም ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት ላይ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የቁጥጥር ሥራውን ሥኬታማ ለማድረግም በሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን የታነጹ፤ በቀናነት ሕብረተሰቡን የሚያገለግሉ ፖራ ሚሊተሪ ኦፊሰሮችን የማፍራቱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ኦፊሰሮችን አሰልጠኖ ከማሰማራት ጀምሮ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና መስጠት ላይ ትኩረት መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በየትኛውም አይነት የብልሹ አሰራር ተግባር ላይ የሚሳተፉና የአሰራር ክፍተት የሚፈጥሩ አመራርና ኦፊሰሮች ላይ አስፈላጊው ርምጃ እንደሚወሰድም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የባለስልጣኑ ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው በበኩላቸው÷ አዲስ አበባ ለኑሮ ምቹና ውብ ከተማ ሆና እንድትቀጥል የሚስተዋሉ የደንብ ጥሰቶችን መከላከል የሁሉም ሕብረተሰብ ድርሻ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ሰልጣኝ አመራሮችና ኦፊሰሮች በቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም ከብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት እንዲሰጡም አሳስበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.