Fana: At a Speed of Life!

ሕንድ ለኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የአቅም ግንባታ ድጋፍ አደርጋለሁ አለች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕንድ መንግሥት በግብርና ኢንቨስትመንት፣ በእርሻ ምርቶች ግብይት እና በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ላይ ለኢትዮጵያ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋገጠ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ከሆኑት አኒል ኩማር ጋር በግብርና ዘርፍ ሀገራቱ በጋራ መሥራት በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የሀገራቱን ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር የሕንድ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር በግብርናው ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ያለውን ፍላጎት ሚኒስትሩ አድንቀዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበውን አመርቂ ውጤት ለማስቀጠልም ኢትዮጵያ ከሕንድ እውቀት እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መቅሰም እንደምትፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

አምባሳደር አኒል ኩማር በበኩላቸው የሕንድ መንግሥት በግብርና ኢንቨስትመንት፣ በእርሻ ምርቶች ግብይት እና በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ላይ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይ በጋራ በሚሠሩ ጉዳዮች ላይም መግባባት ላይ መድረሳቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.