በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን 4 ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በዘንድሮው ዓመት ለመትከል ከታቀደው 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ውስጥ እስካሁን 4 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የተፈጥሮ ሃብት መመናመንና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመከላከል የግብርና ምርታማነት ለማሳደግና ዘላቂነት ያለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተመላክቷል፡፡
በዛሬው እለት የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በሸገር ከተማ አስተዳደር በለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ ለገዳዲ ወረዳ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ዘንድሮ ለመትከል ከታቀደው 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ውስጥ እስካሁን ድረስ በመላ ሀገሪቱ 4 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል፡፡
ዕቅዱን ለማሳካት በቀጣይ በስፋት ችግኝ ተከላ ማካሄድ እንደሚገባ ያሳሰቡት ሚኒስትሩ፤ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር መጠበቅና መንከባከብ እንደሚያስፈልግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡