Fana: At a Speed of Life!

አየርላንድ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት ለመደገፍ ቁርጠኛ ነኝ አለች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አየርላንድ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት በተለያዩ ዘርፎች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን አስታወቀች፡፡

የአየርላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የመከላከያ ሚኒስትር ሚካኤል ማርቲን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ጎብኝተዋል፡፡

ከጉብኝታቸው በኋላም በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘውን ሀገራዊ ምክክር ሂደት አሁናዊ ተግባራት በተመለከተ በኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጻ እና ማብራርያ ተሰጥቷል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የአየርላንድን የሰላም ግንባታ ሂደት ተሞክሮ አስረድተዋል፡፡

በሂደቱም የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ብዘኃነትን የማስተናገድ ፈቃደኝነት ለሀገራዊ ምክክር እና ለሰላም ግንባታ ሂደት የነበራቸውን ጉልህ ሚና አብራርተዋል፡፡

በሀገራቸው በተደረጉ የሰላም ግንባታ ሂደቶች ሴቶች የሂደቱ ዋነኛ ተሳታፊ እና ከዋኝ መደረጋቸው ሂደቱን ውጤታማ እንዳደረገውም አንስተዋል፡፡

አየርላንድ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት በተለያዩ ዘርፎች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.