Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 3 ዓመታት በሲዳማ ክልል 22 የመስኖ ልማት አውታሮች ተገነቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ 22 የመስኖ ልማት አውታሮች ተገንብተዋል ተባለ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ በተለይም በቆላማ አካባቢዎች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡

በዚህም ዓመቱን ሙሉ ማምረት የሚያስችሉ ዘመናዊ የመስኖ ልማት አውታሮች እየተገነቡ መሆናቸውን በመግለጽ፥ ለሽራም ክልሉ በየዓመቱ ከ300 ሚሊየን ብር ያላነሰ በጀት እየመደበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሰፋፊ መሬቶችን ማልማት የሚችሉ በርካታ የመስኖ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ በበጋ ወራት ለአገልግሎት የሚበቁ አዳዲስ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው÷ እነዚህ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ የክልሉን የግብርና ምርታማነት ያሳድጉታል ነው ያሉት፡፡

ይህም ገበያን ከማረጋጋት ባሻገር የማይበገር ኢኮኖሚን በመገንባት ከድህነት ለመውጣት ቁልፍ ነው ብለዋል።

የክልሉ መስኖ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር መስፍን በላይ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ እያንዳንዳቸው ከ150 እስከ 250 ሔክታር ማልማት የሚያስችሉ 22 የመስኖ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ተጨማሪ 4 ሺህ 500 ሔክታር መሬት ማልማት እንደሚያስችሉና በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.