አቶ አረጋ ከተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አመራሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) የኢትዮጵያ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
አቶ አረጋ÷ ውይይቱ ኦቻ ዘንድሮ በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የነበረው አፈጻጸም የተገመገመበት እና በቀጣይ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የተመከረበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኦቻ ለተፈናቃይ ወገኖች እና በድርቅ ለተጎዱ የክልሉ አካባቢዎች አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ አድርጓል ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ÷ ዛሬ ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂ ልማት ላይ አብሮ መሥራት የሚያስችል ውይይት አድርገናል ብለዋል።
በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፖል ሃንድሊ÷ ውይይቱ ያለፈውን አፈጻጸም ገምግሞ ለቀጣይ ዓመት የትኩረት መስክን መለየት ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል።
ኦቻ ባለፈው ዓመት አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ድርቅ እና መሰል ችግሮችን ተከትሎ ለሚፈጠር ሰብዓዊ ቀውስ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ስለመደረጉ ማስረዳታቸውንም አሚኮ ዘግቧል፡፡
ዳይሬክተሩ ከርዕሰ መሥተዳድሩ ጋር በነበራቸው ውይይት የክልሉ መንግሥት ከአስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂ የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እንደጠየቃቸው ነው የገለጹት።
በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር ከተፈታ በክልሉ ዘላቂ ልማት ላይ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ዝግጅት ይደረጋልም ብለዋል።