ሕገ-ወጥነትን መቆጣጠር የፖለቲካ መሪዎች ተቀዳሚ ተልዕኮ ሊሆን እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በየደረጃው የሚገኙ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ ተቋማት ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት በማክሮ ኢኮኖሚ የትኩረት ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ነው።
በምክክር መድረኩ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ ልማት ቢሮ ሃላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር)፣ ከዞን፣ ከተማ አሥተዳደር እና ወረዳዎች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮችም ተሳትፈዋል፡፡
አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ላለፉት ዓመታት በግጭት ውስጥ የቆየ ክልል መሆኑን ጠቁመው÷ ሃብት መፍጠር፣ ማሠባሠብና ገቢ ማመንጨት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ምርታማነትን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን እና ከምርት የሚገኝ ገቢ ላይ ትኩረት መስጠት አንደሚገባም አንስተዋል።
ክልሉ ላለፉት ዓመታት የገጠመው ችግር ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኘው ሃብት ሲያመነጭ እና ሃይል ሲያሠባሥብ ነው ያሉት ሃላፊው÷ለዚህ ደግሞ ሕገ ወጥነትን መከላከልና መቆጣጠር የፖለቲካ መሪዎች ተቀዳሚ ተልዕኮ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ኢንዱስትሪን ማስፋፋትና ከተሜነትን ማዘመን የሚቻለው ሕገ ወጥነትን በመከላከል በመሆኑ በየደረጃው ያለው መሪ ለተፈጻሚነቱ በትጋት እንዲሠራ ማሳሰባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡