በንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ ያካተተ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በመድረኩ÷ የንጽህና መጠበቂያ ምርት በሀገር ውስጥ እንዲመረትና ተደራሽ እንዲሆን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ማቀናጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በፈረንሳይ የልማት ድርጅት ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ድጋፍ ይጠበቃል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው÷ የንፅህና መጠበቂያ እጦት እስከ ጤና እክል የሚያደርስ መሆኑን ጠቅሰው ልዩ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
መድረኩ በሕግ ቁጥጥር፣ በፋይናንስ፣ በስርጭት አውታሮች እንዲሁም በግንዛቤ እና ግንኙነት ሂደት ውስጥ ያሉትን መሰናክሎች በመለየት መፍትሔ ለማመላከት ያለመ ነው ተብሏል፡፡