የድሬዳዋ አስተዳደር ከ9 ቢሊየን ብር በላይ በጀት አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጉባኤ ከ9 ቢሊየን ብር በላይ በጀት በማፅደቅ ተጠናቋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የዳኞች ሹመትና ረቂቅ አዋጆችን እንዲሁም ከ9 ቢሊየን 566 ሚሊየን ብር በላይ በጀት አፅድቋል።
የፀደቀው በጀትም በዓመቱ ከአስተዳደሩ ከሚሰበሰብ 6 ቢሊየን 550 ሚሊየን ብር እና ከፌዴራል መንግስት የተገኘ 2 ቢሊየን 34 ሚሊየን ብር የበጀት ድጎማ እንዲሁም 801 ሚሊየን ብር ከተለያዩ የልማት አጋራት ለድህነት ቅነሳ ማስፈፀሚያ የተመደበ መሆኑም ተገልጿል።
ከፀደቀው በጀት ውስጥ 58 በመቶው ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያነት የተመደበ ሲሆን÷ ቀሪው 42 በመቶው ደግሞ ለመደበኛ በጀት እንደሚውልም ተገልጿል።
ዘንድሮ የፀደቀው በጀት ከአምናው ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ19 በመቶ ብልጫ እንዳለው መገለጹንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡