ያልተገባ ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ እንደሚቀጥል ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምርት በሚደብቁና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የድሬዳዋ አሥተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።
ተግባራዊ የሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲን ተከትሎ አንዳንድ የንግዱ ማኅበረሰብ በግብይት ወቅት ሕገ-ወጥ ተግባር በመፈጸምና በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የኑሮ ውድነትን እያባባሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ፖሊሲው ከመተግበሩ በፊት ያስገቧቸውን ሸቀጦች ሳይቀር በመጋዘን በማከማቸት የንግድ ሂደቱን በሚያውኩ ነጋዴዎች ላይ እየተወሰደ የሚገኘው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ከፖሊሲው በፊት ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የምግብ ሸቀጦችን ደብቀውና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አድርገው የተገኙ 340 ሱቆችና 97 መጋዘኖች እንዲታሸጉ ተደርጓል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከችርቻሮ እስከ ከፍተኛ አስመጪ ያሉ የንግዱ ማኅበረሰብ ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓቱን ጠብቀው ሕዝብን ማገልገል እንደሚገባቸው ከንቲባው አሳስበዋል፡፡