Fana: At a Speed of Life!

ልዩነት ፈጣሪው ኮከብ…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7 ፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)ለአንድ ወር ያህል በአሜሪካ ሲካሄድ የቆየው የዓለም ክለቦች ዋንጫ ቼልሲን ሻምፒዮን በማድረግ ትናንት ምሽት ፍጻሜውን አግኝቷል።

በውድድሩ ሁለቱን የማድሪድ ክለቦች በተመሳሳይ 4 ለ 0 በማሸነፍ ጭምር 16 ግቦችን በማስቆጠር በሚያስደንቅ ብቃት ለፍጻሜው የደረሰው ፒኤስጂ በመጨረሻም ለቼልሲ እጅ ሰጥቷል።

ባየርን ሙኒክ፣ ሪያል ማድሪድ፣ አትሌቲኮ ማድሪድን ሲያሸንፍ አንድም ግብ ያላስተናገደው የፓሪሱ ክለብ ከትናንት ምሽቱ የፍጻሜ ጨዋታ በፊት በውድድሩ ያስተናገደው ግብ አንድ ብቻ ነበር። ሆኖም የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ በውጤታማ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ባስቆጠራቸው 3 ግቦች የማይቀመስ የነበረውን ፒኤስጂ በመርታት ሻምፒዮን ሆኗል።

ግብ ለማስቆጠር የማይታክቱ በሚል በበርካቶች ሲሞካሹ የሰነበቱት የፓሪሱ ክለብ ከዋክብት በትናንቱ የሜት ላይፍ የፍጻሜ ፍልሚያ በግብ ፊት ደብዝዘው አምሽተዋል። በዚህም ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ሮበርት ሳንቼዝ ያለቀላቸውን ግቦች በማምከን መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል።

በቼልሲ ድንቅ እንቅስቃሴ ውስጥ የእንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ኮል ፓልመር ሚና ወሳኝ ነበር። በምሽቱ ጨዋታ ደምቆ ያመሸው የ23 ዓመቱ ኮከብ ለሰማያዊዎቹ ጣፋጭ ድል የተገኘባቸውን 2 ግቦች ሲያስቆጥር፥ አዲሱ የቼልሲ ፈራሚ ዦአዎ ፔድሮ ያስቆጠራትን ግብ አመቻችቶ አቀብሏል።

ለእግር ኳስ ባደላው ልጅነቱ የዋይን ሩኒ አድናቂና የማንቼስተር ዩናይትድ ደጋፊ የነበረው ፓልመር ገና ታዳጊ ሳለ እግር ኳስ ተጫዋች መሆንን አብዝቶ ይመኝ ነበር። በማንቼስተር ሲቲ በኩል ፕሮፌሽናል እግር ኳስን የጀመረው ፓልመር፥ በኢቲሃድ እምብዛም የመሰለፍ እድል ባለማግኘቱ በ2023/24 ቼልሲን ተቀላቀለ።

በመጀመሪያ አመት የስታምፎርድ ብሪጅ ቆይታው በሁሉም ውድድሮች በ46 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ መጫወት ችሏል። በእነዚህ ጨዋታዎች 27 ግቦችን ያስቆጠረው እንግሊዛዊ ኮከብ 15 ግብ የሆኑ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ አመቻችቶ አቀብሏል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በመጀመሪያው አመት የለንደን ቆይታው ባሳየው ብቃት ልክ ውጤታማ ዓመት ባያሳልፍም በተለይ በትናንቱ ፍጻሜ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል።

ፓልመር ማንቼስተር ሲቲን ለቆ ቼልሲን በተቀላቀለበት የመጀመሪያ ዓመት የክለቡ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች እንዲሁም የቼልሲ ተጫዋቾች የዓመቱ ምርጥ በመሆን ተመርጧል።

በትናንት ምሽቱ ጨዋታ ያስመለከተው ብቃት የጨዋታው ኮከብ ሆኖ እንዲመረጥ አስችሎታል። ፓልመር የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች ተብሎም ተመርጧል። በቀጣይ በቼልሲ ቤት ይበልጥ እየደመቁ እንደሚቀጥሉ ከሚጠበቁ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ለኢንዞ ማሬስካ ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል።

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.