የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስምሪቶች ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና ነበራቸው – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተቋሙ ስምሪቶች ሀገራዊ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው ÷ የአገልግሎቱ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተለያዩ የሥራ ክፍሎችን ተዘዋውረው በመጎብኘት በቀጣይ ስምሪቶች ዙሪያ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ተቋሙ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ የሰላም መደፍረሶችና ግጭቶች እንዲፈቱ ኅብረተሰቡም በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በተከናወኑ ስምሪቶችና ኦፕሬሽኖች ጸረ-ሰላም ኃይሎችና ጽንፈኞች የሀገርንና የህዝብን ሰላምና መረጋጋት ለማወክ የሚሠሯቸው ሴራዎች መክሸፋቸውን በመግለጽ ፤ በዚህም የጸጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ማረጋጋትና ሀገርን ማጽናት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች የነበራቸው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ነበር ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ÷ የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ሥራን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
የላቀ የመፈጸም አቅም ያለው ተቋም እየተገነባ መሆኑን እንዲሁም ሀገራዊ ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ የሚያበረክተው የማይተካ ሚና ጎልቶ እየታየ በመሆኑ ይህን ያረጋገጠው ሪፎርም ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት እየተቃኘ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች በ2016 የበጀት ዓመት የነበራቸው የላቀ አፈጻጸም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሥራ ስምሪት መስጠታቸው ተመላክቷል፡፡