በገበታ ለሀገር በኮይሻ ፕሮጀክት ውስጥ ከሚለሙ የቱሪዝም መስኅቦች አንዱ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ነው።
👉 በ1997 ዓ.ም በብሔራዊ ፓርክነት የተቋቋመው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኝ ሲሆን÷ 1 ሺህ 410 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አለው፡፡
👉 በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ዝሆንን ጨምሮ ከሌሎች ግዙፍ አጥቢ እንስሳት እስከ አነስተኛ ነፍሳት ይገኛሉ፡፡
👉 በተፈጥሮ ሀብቱ ብዛትና መጠነ-ስፋቱ እንዲሁም በማራኪ ውበቱ የተነሳ በርካቶች ፓርኩን “ምድረ-ገነት” ይሉታል፡፡
👉 ከአዲስ አበባ 450 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ፓርኩ÷ የአፍሪካ ዝሆኖች የሚገማሸሩበት፣ የጎሽ መንጋ የሚራወጥበት፣ አንበሳ እና ነብርን ጨምሮ 57 ዝርያ ያላቸው አጥቢ የዱር እንስሳት የሚርመሰመሱበት ነው።
👉 ብርቅዬ የአዕዋፍና የዓሣ ዝርያዎች፣ ፍል ውኃዎች፣ ፏፏቴዎች፣ ዋሻዎችና ሌሎች የተፈጥሮ ፀጋዎችን የተቸረ የመስኅብ ስፍራም ነው።
👉 የመካከለኛው ኦሞ ሸለቆ አረንጓዴያማው ጌጥ ጨበራ ጩርጩራ ወደ 50 የሚጠጉ ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ወንዞች መነሻ፣ በዕፅዋት ሥነ-ምኅዳሩም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ጨምሮ አያሌ የዕፅዋት ብዝኃ-ሕይወትን የለበሰ ተፈጥሯዊ ፀጋ ነው።
👉 የተራራና የዝቅተኛ ስፍራዎች መገኛ በመሆኑ በከፍታ ቦታ የሚገኝ ቅዝቃዜን በዝቅተኛ ቦታ የሚገኝ ሙቀትን የያዘ ስፍራ ነው።
👉 ከወንዞቹ መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ሾሺማ እየተባለ የሚጠራው ወንዝ ሲሆን÷ በፓርኩ ውስጥ ያለው የወንዝ ፍሰት ለስፍራው ተጨማሪ ውበት ሆኖታል።
👉 ከ49 በላይ ወንዞች ከፓርኩ በመነሳት ወደ ኦሞ ወንዝ ይገባሉ።
👉 የሐይቆች ምድር የሚባለው ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ ስድስት ሐይቆችን የያዘ ሲሆን÷ ለአብነትም ቡሎ፣ ባሄ፣ ከሪበላ፣ ሽታ፣ ቆቃ እና ጮፎሬ ከሐይቆቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
👉 ከአምስቱ ሐይቆች በአንዱ በሳይንሳዊ ስሙ ጋራ ጨበራ (Gara Chebra) የተሰኘ ብርቅዬ የአሳ ዝርያ ይገኛል።
👉 ከፏፏቴዎቹ መካከልም ባርቦ ፏፏቴ አንዱ ሲሆን÷ የፏፏቴው ድምጽ ለፓርኩ ተጨማሪ ድምቀት ሆኖታል።
👉 ፓርኩ ያለው የደን ሽፋን ሰፊና ጉልህ የሚባል ሲሆን÷ የሰው ሰፈራና እርሻ በውስጡ አለመኖሩ ለዚህ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይነገራል።
👉 በተፈጥሮ መዝናናት፣ ፀጥታና የመንፈስ መረጋጋትን የሚፈልጉ ሰዎች የሚመርጡት ፓርክ ነው ይባልለታል።
👉 ፓርኩ እምቅ የሚባሉ የቱሪዝም ሀብቶችን በውስጡ ቢይዝም÷ በመሰረተ-ልማት ችግሮች ምክንያት በሚገባው ልክ አለመጎብኘቱና አለመተዋወቁ ሲገለጽ ቆይቷል።
👉 የገበታ ለሀገር አካል የሆነው የኮይሻ ፕሮጀክትም ፓርኩን ለመጎብኘት የሚያስችል መሰረተ-ልማት በማሟላት የአካባቢውን የቱሪዝም ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል።
የመሰረተ-ልማት ግንባታዎቹ የፓርኩን ተፈጥሮ ሳይረብሽ ከፓርኩ ውጪ የሚከናወን ሲሆን÷ ይህም ቱሪስቶች ፓርኩን በቀላሉ እንዲጎበኙት የሚያስችል ነው።