የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ አየር መንገድን በ1 ወር ውስጥ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት ተጠናቋል – አቶ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ አየር መንገድ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ በራዕዩ መሰረት ሊደርስበት ያቀደው ደረጃ ላይ ለመድረስ በሁሉም አቅጣጫ በፈጣን የእድገት መንገድ ላይ ይገኛል።
በተለይ የአፍሪካ አየር መንገዶችን በማቋቋም ረገድ አየር መንገዱ ሰፊ ተሞክሮ እንዳለውና በቅርቡም በኮንጎ ኪንሻሳ አዲስ አየር መንገድ ለማቋቋም ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ እንዲሁም የኮንጎ መንግስት 51 በመቶ ድርሻ በመያዝ በመጪው ሕዳር ወር መቀመጫውን ኪንሻሳ ላይ ያደረገ አዲስ አየር መንገድ ወደ ስራ እንደሚገባ ነው ያስታወቁት።
የኤር ኮንጎን አየር መንገድ የማስተዳደር ሃላፊነትም ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደሚሆን አስታውቀዋል።
አየር መንገዱ የመጀመሪያ አገልግሎቱን በሁለት አውሮፕላኖች በሀገር ውስጥ በረራ እንደሚጀምርና ከስድስት ወር በኋላ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር በመጨመር ወደ ጎረቤት ሀገራት በረራ ይጀምራል ብለዋል።
የኮንጎ ህዝብ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ በሀገሪቱ ያለው የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት የላቀ መሆኑን አንስተው፤ ይህም ለአየር መንገዱ ገበያ ትርፋማነት ወሳኝ ስራ እንደሚሆን አክለዋል።
በመሆኑም አየር መንገዱን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች አየር መንገዶቻቸውን እንድናቋቁምላቸው ጥያቄ እያቀረቡ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ከሀገራቱ ጋር ለመስራት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ እንደሆነም ጠቁመዋል።
አየር መንገዱ በቶጎ አየር መንገድ አስካይ ኤር ዌይስ፣ በማላዊ ማላዊ ኤርዌይስ፣ በዛምቢያ ዛምቢያ ኤር ዌይስን በማቋቋም ድርሻ ይዞ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።