ኢትዮ ቴሌኮም 5ጂ የሞባይል አገልግሎትን በቢሾፍቱ ከተማ አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የአምስተኛው ትውልድ (5ጂ) የሞባይል አገልግሎትን በቢሾፍቱ ከተማ አስጀምሯል፡፡
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ፣ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ፣ አባ ገዳዎች፣ሃደ ሲንቄዎችና የከተማው ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ ተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩ ፍሬህይወት ታምሩ÷ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድርግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ አንዱ አካል የሆነው የ5ጂ ኢንተርኔትም ለቢሾፍቱ ከተማ በውበቷ ላይ ሌላ የቴክኖሎጂ አቅም ሊፈጥርላት ዛሬ በከተማዋ በይፋ መጀመሩንም አብስረዋል፡፡
ይህም ከተማዋ የበለጠ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን እንደሚረዳትም ነው ዋና ስራ አስፈፃሚዋ የገለፁት፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም የ5ጂ ኔትወርክ ተግባራዊ ማድረግ የኔትዎርክ መጨናነቅን በመቀነስ ደንበኞች ጥራት ያለውና ፈጣን የኮሙኒኬሽን፣ ዲጂታል ሶሉሽኖችና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ህይወታቸውን እንዲያቀሉ ከማስቻል ባሻገር የኦንላይን ትምህርት፣ ስልጠና፣ መረጃና የመዝናኛ አገልግሎት አቅርቦትን ያሳድጋል፡፡
እንዲሁም የይዘት ፈጠራ ፣ ለጀማሪ የሶፍትዌር አበልጻጊዎች ኢኖቬሽን እና የሥራ ፈጠራን በማበረታታት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል፤ የስማርት ስልክ ስርዓትን ለመጨመር መደላድል በመፍጠር የዲጂታል ሊትሬሲን በማሳደግ እና የዲጂታል ክፍተትን በማጥበብ አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባትም አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሏል፡፡
የ5ኛው ትውልድ ቴክኖሎጂ እስከ 10 ጊጋ ባይት በሰከንድ የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ዓለም የደረሰበት ዘመናዊ የገመድ አልባ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ሲሆን÷ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን እጅግ በላቀ ሁኔታ በመቀነስ ረገድ ወደ 1ሚሊ ሰከንድ የሚያደርስ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
የ5ጂ የሞባይል አገልግሎት ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሆሳዕና እና አርባ ምንጭ ከተሞች እና አካባቢያቸው ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል፡፡
በፌቨን ቢሻው