የኦሮሚያ ክልል አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖች በንጹሀን ላይ የሚፈጽሙትን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት አወገዘ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖች በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት አወገዘ።
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ በሰጡት መግለጫ÷ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ የሚወገዝ ድርጊት ነው ብለዋል።
የሸኔ አሸባሪ ቡድንና ጽንፈኛው ቡድን የተለያየ ቋንቋ ይናገሩ እንጂ ድርጊታቸው ተመሳሳይ ነው በማለት ገልጸው÷ ቡድኖቹ በህዝቡ መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር አስነዋሪ ድርጊቶች እየፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል።
አሸባሪ የሸኔ ቡድን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጽመው ድርጊት የህዝብ ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅና ልማት እንዲደናቀፍ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ራሱን ፋኖ እያለ የሚጠራው ጽንፈኛው ቡድን የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች በንጹሀን ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል።
የክልሉ መንግስት በቡድኖቹ የሚፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትን በማውገዝ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የህግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መጠቆማቸው የዘገበው ኢዜአ ነው።
በአሸባሪው ሸኔ ላይም ተከታታይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰው÷ የሰላም መንገድ የመረጡት የቡድኑ አባላት እጃቸውን እየሰጡ ነው ብለዋል።
ህዝቡ አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖችን ለማስወገድ በጋራ እንዲቆምም መልዕክት አስተላልፈዋል።