Fana: At a Speed of Life!

ክልሉ ከ8 ሚሊየን ኩንታል የሚልቅ ማዳበሪያ ለማሰራጨት ዝግጅት እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017/18 የምርት ዘመን ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በ2016/17 የምርት ዘመን የማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት እንዲሳካ ላደረጉ አካላት የዕውቅና መርሐ-ግብር ተካሂዷል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን በዚሁ ወቅት÷ በተያዘው የምርት ዘመን የማዳበሪያ ስርጭቱ ውጤታማ እንዲሆን ባለ ድርሻ አካላት በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የግብዓት አቅርቦትና አጠቃቀም በማምረት አቅም ላይ ተጽዕኖ ስላለው ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ባለፈው የምርት ዘመን ያጋጠሙ ክፍተቶችን በማረም በአቅርቦቱ ልክ ውጤታማ ስርጭት እንዲኖር በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊው ድረስ ሳኅሉ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ባለፈው የምርት ዘመንም 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት መገኘቱን እና ከ7 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የሚልቀው መሠራጨቱ አስታውሰዋል፡፡

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.