Fana: At a Speed of Life!

ገዢ ትርክትን በማጎልበት ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ገዢ ትርክትን በማጎልበት ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት ተከበረ ።

በአከባበር ሥነ-ሥርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ፣ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የሕዝብ ተወካዮቸ ም/ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እና የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ተገኝተዋል፡፡

እንዲሁም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች፣ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በበዓሉ ታድመዋል፡፡

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ ገዢ ትርክትን በማጎልበት ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሕብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት እና ለማጽናትም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መከበር ሚናው የጎላ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ትልቅ መጽሃፍ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በውስጧ በርካታ ባሕሎች ፣ እሴቶች፣ እውቀቶችና ጥበቦች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

አንድ መጽሐፍ ብቻውን ሙሉ እንደማይሆን ሁሉ የኢትዮጵያ ብሔሮችም አብሮነትን በማጎልበት ጉድለቶችን መሙላት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ልባችን ወደ ሰላም በመመለስ ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማበልጸግ በጋራ እና በትብብር እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ተቀድታ የማታልቅ በሕር በመሆኗ በቁንጽል እውቀት ከመበየን ይልቅ በቅርበት ሆኖ ማጥናት፣ መመራመርና ማወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

በጋራ ስንቆም ውብና ጠንካራ እንሆናለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ (ዶ /ር)÷ አብሮነታችን በምንም ሁኔታ የማንሸረሽር ሕዝቦች እንሁን ሲሉም አስገንዝበዋል፡:

በመደመር እሳቤ በህብረ ብሄራዊ ትርክት በጋራ ለመቆም ሁሉም ዜጋ እንዲወስንም ጠይቀዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ከግልና ከአንድ አካባቢ መሻትና ፍላጎት ይልቅ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና እድገት በጋራ መቆም ክብር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች ከጦርነት ሰላም ይሻላል ብለው ወደ ሰላም መምጣታቸውን አስታውሰው÷ ይህን መልካም ጅማሮ በኦሮሚያ፣ አማራ እና በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ታጣቂ ወንድሞች እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.