የደቡብ ዕዝ የተወርዋሪ ኮርን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ዕዝ የተወርዋሪ ኮር አኩሪ የድል ልምዶች በተሞክሮ በመውሰድ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን የኮሩ አዛዥ ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋዬ ገለጹ፡፡
የደቡብ ዕዝ የተወርዋሪ ኮከብ ኮር የሦስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል “ተወርዋሪ ድል አብሳሪ” በሚል መሪ ሐሳብ ተከብሯል፡፡
ዛሬ በተካሄደው የበዓሉ ማጠናቀቂያ ዝግጅት ላይ የኮሩ አዛዥ ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋዬ፥ ኮሩ በኢትዮጵያ ከተቋቋሙት አንጋፋ ክፍለጦሮች በተውጣጡ አመራሮች የተመሰረተና ጀግንነቱን የወረሰ ነው ብለዋል፡፡
ያለፉትን አኩሪ የድል ልምዶች በተሞክሮ በመውሰድም ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሠራ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
ኮሩ በአነስተኛ የሰው ኃይልና በትንሽ ኪሳራ ከፍተኛ ድል የማስመዝገብ ሚስጢሩ÷ እየተዋጋ በመሰልጠን ፤ እየሰለጠነ በመዋጋቱ ነው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በዓሉን ስናከብር የጀግኖችን መስዋዕትነት እየዘከርንና ዳግም ቃልኪዳናችንን እያደስን በማስቀጠል ነውም ብለዋል፡፡
በዕለቱ ለጀግኖች ሰማዕታት ቤተሰቦች፣ ጉዳት ለደረሰባቸው የሠራዊት አባላትና ለኮሩ የግዳጅ አፈፃፀም ድጋፍ ላደረጉ አካላት ዕውቅና ሽልማት ተሰጥቷል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ