ለሁላችን የሆነች ኢትዮጵያን እናፀናለን – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከስሜትና ጠርዝ ከረገጠ አዝማሚያ ታቅበን አንድነታችንን በማጠናከር ከሁላችን ለሁላችን የሆነች ኢትዮጵያን እናፀናለን ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባባሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
አቶ አደም ለ19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ ኢትዮጵያውያን በመገናኘት ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና ታሪካቸውን ለመተዋዋቅና ለመማማር በሚያስችል መልኩ ለሚገልፁበት፣ ትስስራቸውንና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ ቃል ኪዳናቸውን ለሚያድሱበት የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
የዘንድሮውን የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በውቢቷ የፍቅር ከተማ አርባምንጭ በድምቀት ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ አክብረናል ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብዝኃ ሐሳብ፣ የብዝኃ አመለካከት፣ የብዝኃ ማንነት ሀገር መሆኗን ማመንና ማስተናገድ መፃኢ የጋራ ዕጣ ፈንታችን ያመረ እንዲሆን ያስችላል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም ከስሜትና ጠርዝ ከረገጠ አዝማሚያ ታቅበን ልዩነቶቻችንን አክብረን አንድነታችንን አጠናክረን ከሁላችን ለሁላችን የሆነች ኢትዮጵያን እናፀናለን ነው ያሉት፡፡
ለጋራ ብልጽግና የተጋመደ ውጥናችንን በጋራ ቃል ኪዳናችን እያፀናን፣ እኩልነት እና አንድነትን በፅኑ መሰረት ላይ በመገንባት እኛ የኢትዮጵያ ልጆች የብልጽግናን ጉዟችንን ማፋጠኑን እንቀጥላለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ይለመልማል፤ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች ያሉት አቶ አደም÷ ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡